ህወሓት ያበደርኩትን ነዳጅ መልሼ ወሰድኩ እንጂ አልዘረፍኩም አለ

ወደ ትግራይ እርዳታ የሚያጓጉዙ የጭነት ተሽከርካሪዎች

የፎቶው ባለመብት, AFP

የምስሉ መግለጫ, ወደ ትግራይ እርዳታ የሚያጓጉዙ የጭነት ተሽከርካሪዎች

ህወሓት ከወራት በፊት ለዓለም ምግብ ፕሮግራም ያበደርኩትን ነዳጅ መልሼ ወስድኩ እንጂ ዘረፋ አልፈጸምኩ አለ።

ህወሓት ይህን ያለው የዓለም ምግብ ፕሮግራም የትግራይ ኃይሎች መቀለ ከሚገኘው ቅጥር ግቢዬ በኃይል ገብተው ከግማሽ ሚሊዮን በላይ ሊትር ነዳጅ ዘርፈዋል ካለ በኋላ ነው።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢዝሊ ነዳጁ በኃይል መወሰዱን “አስደንጋጭ እና አሳፋሪ” በማለት ገልጸው ነዳጁ “አሁኑኑ” ይመለስ ሲሉ በአጽንኦት ጠይቀው ነበር።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ይህን ይበል እንጂ የትግራይ አመራሮች የቀረበባቸውን ክስ ተከትሎ ባወጡት መግለጫ ዋና ዳይሬክተር ዴቪድ ቢዝሊን እና የዓለም ምግብ ፕሮግራምን አጥብቀው ተችተዋል።  

ዋና ዳይሬክተሩ በተጨማሪ የተባበሩት መንግሥታት ድርጅት ዋና ፀሐፊ ቃል አቀባይ ስቴፋን ዱጃሪክም የትግራይ ኃይሎች መቀለ ውስጥ ወደ ሚገኘው የዓለም ምግብ ፕሮግራም መጋዘን በኃይል ገብተው ዘረፋ ፈጽመዋል ብለዋል።

በዚህም 570,000 ሊትር ነዳጅ የጫኑ 12 ቦቴዎች መዘረፋቸውና የድርጅቱ ሠራተኞች ይህንን ድርጊት ለማስቆም ቢሞክሩም እንዳልተሳካላቸው አመልክተዋል።

ዋና ዳይሬክተር ዲቪድ ቢዝሊ “የትግራይ መንግሥት ‘ሰርቋል’ በማለት መክሰሳቸውን እጅጉን ረብሾናል” ብለዋል የትግራይ አመራሮች በመግለጫቸው።

ዋና ዳይሬክተሩ መሰል አስተያየት ከመስጠጣቸው በፊት ዝርዝር ሁኔታውን ማጣራት ነበረባቸው ያለው መግለጫው፤ የትግራይ ክልል አመራር ነዳጅ አለመስረቃቸውን፤ ይልቁንም ለዓለም ምግብ ፕሮግራም ከ600 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ማበደራቸውን በመግለጫው ተጠቅሷል።

“በነበረን ስምምነት መሠረት ለዓለም ምግብ ፕሮግራም ያበደርነውን ከ600 ሺህ ሊትር በላይ ነዳጅ ተመላሽ እንዲሆን ነው የጠየቅነው።”

የትግራይ ክልል አስተዳዳሪዎች በመግለጫው ላይ ከዓለም ምግብ ፕሮግራም የወሰድነው ነዳጅ እንደ ሆስፒታል፣ ክሊኒክ እና ሌሎች የጤና ማዕከላትን ለማንቀሳቀስ ጥቅም ላይ ይውሏል ብለዋል።

የትግራይ ኃይሎች ይህን ይበሉ እንጂ የፌደራሉ መንግሥት የነዳጅ ‘ዝርፊያውን’ በተመለከተ ባወጣው መግለጫ ላይ፤ የትግራይ ኃይሎች ነዳጁን መውሰድ ያስፈለጋቸው በቆቦና በአካባቢው ለከፈቱት ጥቃት ማስፈጸሚያ እንዲሆናቸው ነው ብሎ ነበር።

ከዚህ በተጨማሪም የመንግሥት ኮሙኒኬሽን ጉዳዮች ጽህፈት ቤት በመግለጫው “. . . ቡድኑ ከፈጸመው ዝርፊያ ባሻገር ድርጊቱን ለማስቆም የሞከሩ የሰብዓዊ እርዳታ ባለሙያዎችንም አስሯል” ብሎ ነበር።

የዓለም ምግብ ፕሮግራም ነዳጅ ተዘርፊያለሁ ማለቱን ተከትሎ የኢትዮጵያ መንግሥት ባወጣው መግለጫ በዓለም አቀፉ ማኅበረሰብ አማካይነት ወደ ትግራይ ክልል የሚገባው ሰብዓዊ ዕርዳታ ለታለመለት ዓላማ እየዋለ ስለመሆኑ ማስተማመኛ ይሰጠኝ ሲል ጠይቋል።

የትግራይ ክልል አስተዳደሪዎች ሐሙስ ነሐሴ 19 አመሻሸ 2014 ዓ.ም. ባወጡት መግለጫ ላይ ከጥቂት ወራት በፊት የዓለም ምግብ ፕሮግራም በነዳጅ እጥረት ምክንያት የምግብ እርዳታ ማከፋፈል ባለመቻሉ ከትግራይ ክልል መንግሥት ነዳጅ መበደሩን የዓለም ምግብ ፕሮግራም ነዳጁን እንደሚመልስ ግንዛቤ ነበር ብለዋል።

ስምምነታችን በጽሑፍ ተሰንዶ ተቀምጧል የሚሉት የትግራይ ክልል አመራሮች፤ አሁን ላይ የዓለም ምግብ ፕሮግራም የተበደረውን ነዳጅ ‘በአይነት መልሼ እንደምከፍል አላውቅም’ ማለቱ ስምምነታችንን የሚጻረር ነው ብለዋል።

የህወሓት መሪዎች የዓለም ምግብ ፕሮግራም ገብቶት የነበረውን ስምምነት በማክበር ያወጣውን ‘እጅግ ጎጂ’ የሆነ አስተያየት እንዲያነሳ ጠይቀዋል።